መድን ገቢው የዚህ ውል አካል በሆኑት የውል መጠየቂያ እና የውል ማረጋገጫ ቅጽ መሠረት ቤት ሰብሮ ለሚፈፀም ዝርፊያ የሚሰጥ የመድን ዋስትና ለመግዛት ጥያቄ በማቅረቡና ተገቢውን አረቦን በመክፈሉ ወይም ለመክፈል በመስማማቱ ዋስትናው የሚሰጠው ሽፋን ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
በዋስትና ዘመኑ ውስጥ የመድን ገቢው የሆነ ወይም በአደራ ወይም በኮሚሽን በመድን ገቢው የተያዘ ንብረት በቅጥር ግቢው ውስጥ እያለ ኃይል በተቀላቀለበት ሁኔታ በመግባት ወይም በመውጣት በሌባ ቢሰረቅ ወይም ለማንኛውም በቅጥር ግቢው ላይ ለደረሰ ጉዳት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የካሣ ክፍያ ለመፈፀም ተስማምቷል፡፡
ካሣ ክፍያ የተጠየቀበት ንብረት በእርግጠኝነት በሌባ ለመጥፋቱ ወይም ለመውደሙ መድን ገቢው ለድርጅቱ መረጃ ማረጋገጫ ካቀረበና መረጃውንም ድርጅቱ ከተቀበለው ድርጅቱ በራሱ ምርጫ በጥሬ ገንዘብ፣ ወደነበረበት በመመለስ፣ በመተካት ወይም በመጠገን በውል ሠንጠረዡ ላይ ለእያንዳንዱ ወይም ለጥቅል ዕቃዎች ከተቀመጠው የዋስትና መጠን የገንዘብ ልክ ያልበለጠ ወይም ባጠቃላይ ዋስትና የተገባለትን ሂሳብ ለመድን ገቢው ይከፍላል፡፡
ማግለያ አንቀጾች
ይህ ውል በሚከተሉት ሁኔታዎች የደረሰን ጉዳት፣ ጥፋት ወይም ውድመት አይሸፍንም፤
1. በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በጦርነት፣ በወረራ፣ በውጭ ጠላት ድርጊት፣ በጥላቻ ወይም በጦርነት መሰል እንቅስቃሴ ጦርነት ቢታወጅም ባይታወጅም፣ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በወታደራዊ አመጽ፣ በሕግ አልበኝነት፣ በሥራ ማቆም አድማ፣ በሕዝብ ብጥብጥ፣ በወታደራዊ ወይም ሕዝባዊ መነሳሳት፣ በውንብድና፣ በአብዮት፣ በሥልጣን ንጥቂያ ወዘተ፣ 2. በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ከማንኛውም የኡ??ክሊየር ነዳጅ መንስኤ ለሆነ ራዲየሽን ወይም በኡ??ክሊየር መንደድ የተነሳ ለሚከሰት የኡ??ክሊየር ብክለት፣ 3. ለጉዳቱ መንስኤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአክሊየር ጦር መሣሪያ አስተዋፅኦ ካለው፣ 4. ጉዳቱ የደረሰው ማንኛውም የመድን ገቢው ቤተሰብ ወይም የሥራ ባልደረባ፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ በቅጥር ግቢው ወይም በሥራው ቦታ እያለ ከሆነ፣ 5. መድን ገቢው ከድርጅቱ የጽሑፍ ማረጋገጫ/ስምምነት ሳያገኝ በቅጥር ግቢው ላይ ለውጥ ካደረገ ወይም እንዲደረግ ከፈቀደ ወይም ጥበቃውን ከለወጠ ወይም ጥበቃው እንዲላላ ካደረገ፣ 6. በእሳት ወይም በፍንዳታ ወይም ይህን ተከትሎ ሊከሰት ለሚችል አደጋና በእሳት መድን ዋስትና ሽፋን ሊሰጠው ለሚችል ጉዳት፣ 7. በመስታወት መሰበር መድን ዋስትና ሊሸፈን ለሚችል ጉዳት፣ ሆኖም ቅጥር ግቢው ሙሉ ለሙሉ ለመኖሪያነት የሚያገለግል ከሆነ ይህ ማግለያ አንቀጽ ተፈፃሚ አይሆንም፣ 8. በዚህ ውል ውስጥ በዝርዝር ተገልፆ እንዲካተት ካልተደረገ በስተቀር በሌላ በማንኛውም የመድን ውል ውስጥ ተጠቅሶ የመድን ዋስትና ለተሰጠው ንብረት፣ 9. በእርባታ እንስሳት፣ በገንዘብ፣ በቼክ፣ በጉዞ ቼክ፣ በአክሲዮን ሰርተፊኬት፣ በቦንድ፣ በቃል ኪዳን ሰነድ፣ በቲኬት፣ በቴምብርና በቴምብር ስብስብ፣ በሜዳሊያዎች፣ የሂሳብ ደብተሮች፣ የኘላን ዝርዝር መግለጫዎች ወዘተ፣ 10. በማንኛውም የዋስትና ዘመን ውስጥ ቅጥር ግቢው በተለይ ለመኖሪያ ቤትነት አገልግሎት ከዋለና ቤቱም በአንድ የዋስትና ዘመን ውስጥ በተከታታይም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት ለዘጠና ቀናት ሳይያዝ ከቆየ፣
ጥቅሞች
ቅጥር ግቢው ሙሉ ለሙሉ የግል የመኖሪያ ቤት ከሆነና የውሉ ማግለያ አንቀጾችና የሚሟሉ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ዋስትና በተሰጠው ንብረት ወይም ከፊል ንብረት ላይ ለሚደርስ ጥፋት ውድመት ወይም ጉዳት ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ሁኔታዎችም ሽፋኑ ይቀጥላል፡፡
ሀ) በቅጥር ግቢው ውስጥ ለመኖሪያ ከሚያገለግለው ቤት ተነጥሎ ለብቻው ቢሮ፣ በረትና ጋራዥ ውስጥ ለተቀመጡ ዋስትና የተገባላቸው ንብረቶች፣ ለ) በማንኛውም የግል መኖሪያቤት፣ ሆቴል፣ ቁርስ ቤት፣ ክለብ ወዘተ መድን ገቢው ወይም ማንኛውም የመድን ገቢው ቤተሰብ በጉዳት፣ ጥፋት ወይም ውድመት ወቅት በጊዜያዊነት የሚኖርበት ከነበረና በማንኛውም የዋስትና ዘመን ውስጥ ቤቱ ለጊዜያዊ መኖሪያነት አገልግሎት የሰጠው ከ9ዐ ቀናት ያልበለጠ ከሆነ፣ ሐ) በማንኛውም ሌላ መኖሪያ ቤት በጊዜያዊነት የተቀመጠ ከሆነ መ) በባንክ ወይም በካዝና የተቀመጠ ከሆነ
የሚሟሉ ሁኔታዎች
1. ይህ ውል፣ ከሰንጠረዡና በተጨማሪ እንዲካተቱ ከተደረጉ ሽፋኖች ጋር እንደ አንድ የኮንትራት ውል ይቆጠራል፡፡ ማንኛውም ቃል ወይም አባባል የተለየ ፍች ከተሰጠው ቃሉ ወይም አባባሉ በተገኘበት ቦታ ሁሉ ያንኑ ፍች ይይዛል፡፡
2. የመድን ውል ተቀባዩ በዚህ ውል ውስጥ እንዲተገበሩ የተጠቀሱትን አንቀጾች በተግባር መተርጐምና በውል መጠየቂያው ቅጽና በዲክላራሲዮኑ ላይ የተሰጡት መልሶች እውነት መሆን ድርጅቱ በዚህ ውል መሠረት ኃላፊነት ወስዶ ክፍያ ከመፈፀሙ በፊት ሊሟሉ የሚነሱ ቀድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በውል መጠየቂያው ቅጽ ወይም በዲክላራሲዮኑ ውስጥ ለድርጅቱ የሚያቀርበውን ማንኛውንም ቁልፍ መረጃዎችን መድን ገቢው ካዛባ ወይም ከደበቀ ይህ ውል ዋጋ እንደሌለው ተቆጥሮ የተከፈለው አረቦን ቀሪ ይሆናል፡፡ በድርጅቱ ኃላፊነት/ስልጣን በተሰጠው ኃላፊ በጽሑፍ ጸድቆ ካልተፈረመበት በስተቀር በዚህ ውል አማካኝነት የሚገኝን ጥቅም ለሌላ ማዛወር ወይም የዚህን ውል አንቀጾች መለወጥ ወይም መሠረዝ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
3. መድን ገቢው የመድን ዋስትና ለተሰጠው ንብረት ደህንነት አስፈላጊውን/ተገቢውን ጥንቃቄ ያደርጋል፤ መድን ገቢው ትክክለኛ የሂሳብ ደብተሮችን እንዲሁም ማንኛውንም ሸቀጣሸቀጥ፣ ለሽያጭ በመጋዘን የተዘጋጁ ዕቃዎችን ወይም ተመሳሳይ ንብረትን ግዢ፣ ሽያጭና ወደ ድርጅቱ የሚገቡትን ወይም የሚወጡትን ንብረቶች በሚመለከት የተሟላና ትክክለኛ መረጃዎች በመመዝገብ ይይዛል፡፡
4. ማንኛውም መድን ገቢው የሚሰጠው ማስታወቂያ ወይም የሚፈጥረው ግን ኙነት (communication)
ሀ) በጽሑፍ መሆን ይኖርበታል፣ ወይም በቃል የተሰጠ ከሆነ ወዲያውኑ በጽሑፍ መረጋገጥ አለበት፡፡ ለ) ለድርጅቱ ዋናው መ/ቤት ወይም በውሉ ላይ ለተጠቀሰው ቅርንጫፍ ይቀርባል፤ ወይም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለድርጅቱ ማንኛውም ቢሮ ወይም ከመድን ገቢው ጋር በተለይ በተደረገ ስምምነት ይህንኑ እንዲያሳውቅ ለተገለፀለት ወገን፣ 5. በዚህ ውል ውስጥ ካሣ የሚያስከፍል ሁኔታ ከተፈጠረ፣ መድን ገቢው ሁኔታውን ሀ) ወዲያውኑ ለድርጅቱ በጽሑፍ ያሳውቃል ለ) ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይምተመሳሳይ ሥልጣን ላለው ያሳውቃል ሐ) ማንኛውም አጥፊ ግለሰብ እንዲያዝና እንዲቀጣ እንዲሁም ዋስትና የተሰጠውንና የተሰረቀውን ንብረት ለማፈላለግና ለማግኘት ተገቢ የሆኑ ማናቸውንም እርምጃዎች ይወስዳል፤ መ) ካሣ የሚያስከፍል ሁኔታ ከተፈጠረ መድን ገቢው ወዲያውኑ ወይም በአሥራ አራት ቀናት ውስጥ በራሱ ወጪ አጠቃላይ ሁኔታውን በዝርዝር፣ የተጐዳውን ንብረት ዋጋና የደረሰውን የጥፋት ወይም የጉዳት መጠን ለድርጅቱ ያሳውቃል፡፡ ሠ) ቫውቸሮች፣ ማረጋገጫዎች፣ መግለጫዎችና ከድርጅቱ ሊጠየቁ የሚችሉ ተገቢ መረጃዎችን አስፈላጊም ከሆነ የካሣ ጥያቄውን የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ዲክላራሲዮን ለድርጅቱ ያቀርባል፡፡ ረ) ወጪው በድርጅቱ ሆኖ የተሰረቀን ንብረት ለማስመለስ ወይም መድን ገቢው በውሉ ላይ ወይም በማንኛውም ሌላ ባለሥልጣን ወይም በሌላ ሰው ላይ ያለውን መብት ለማስከበር እንዲችል ማንኛውም የጉዳት ካሣ በድርጅቱ ቢከፈልም ባይከፈልም መድን ገቢው ተገቢውን ድጋፍ ሁሉ ለድርጅቱ ይሰጣል፡፡
የካሣ ጥያቄው በማንኛውም መንገድ የተጭበረበረ ከሆነ ወይም መድን ገቢው ወይም በእሱ ምትክ ማንኛውም ሰው በዚህ ውል መሠረት ጥቅም ለማግኘት የማጭበርበር መንገድ ከተጠቀመ፤ ማንኛውም ጥቅም ወይም ማንኛውም ለዚሁ ተብለው የተፈፀሙ ክፍያዎች ይሠረዛሉ፡፡
6. ዋስትና በተሰጠው ንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ድርጅቱ በማንኛውም ጊዜ ቅጥር ግቢው ውስጥ ገብቶ የሚመለከተው” ንብረት ይይዛል ቅሪቱን ይጠብቃል፡፡ ሆኖም ይህ እንዳይከናወን መድን ገቢው ወይም በእርሱ ምትክ ማንኛውም ሰው ድርጅቱን ካገደ ወይም ከከለከለ በዚህ ውል ላይ ያሉት ጥቅሞች በሙሉ ቀሪ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ውል መሠረት ለማንኛውም ካሣ ጥያቄ ክፍያ ከተፈፀመ፣ ክፍያ የተፈፀመለት ንብረት የድርጅቱ ይሆናል፡፡
7. በዚህ ውል ውስጥ ሽፋን በተሰጠው ንብረት ላይ ማንኛውም ጥፋት ወይም ጉዳት እንደደረሰበት ጥቅል የንብረቱ ዋጋ መድን ገቢው ዋስትና ከገባለት ዋጋ በላይ ከሆነ መድን ገቢው ለልዩነቱ የራሱ መድን ሰጭ ሆኖ ይቆጠራል፣ የጉዳቱንም መቶኛ ይሸፍናል፡፡ ዋስትና ከተሰጠው ንብረት ውስጥ ማንኛውም አንድ ዕቃ አማካይ ስሌት /average/ የሚመለከተው ከሆነ ለዚሁ ዕቃ የተለየ ዋስትና እንደተሰጠው ይቆጠራል፡፡
8. በዚህ ውል መሠረት ዋስትና በተሰጠው ማንኛውም ንብረት ላይ ማንኛውም ጥፋት ወይም ጉዳት በደረሰበት ወቅት በመድን ገቢው ወይም በሱ ምትክ በዚህ ውል ካሣ የተጠየቀበትን ንብረት ሌላ ዋስትና ገዝተውለት ከሆነ ድርጅቱ በስሌት የሚደርስበትን በመቶኛ ድርሻ ከመሸፈን በስተቀር ከዚያ በላይ የመክፈል ወይም የማዋጣት ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡
9. በአንድ የዋስትና ዘመን ውስጥ በየጊዜው በዚህ ውል መሠረት የሚከፈሉ ክፍያዎች ሁሉ ዋስትና የተገባለትን የዋስትና ገንዘብ መጠን እየቀነሱት ከሄዱና ማንኛውም ተከታታይ ካሣ የሚያስከፍል አደጋ ከተፈጠረ በድርጅቱ የሚከፈለው ጠቅላላ ሂሳብ በምንም ምክንያት መጀመሪያ ዋስትና ከተገባለት ዋጋ በላይ አይሆንም በመድን ገቢው ጥያቄ የጠፋው ወይም የተጐዳው ንብረት በሌላ ንብረት የሚተካ ከሆነ ተገቢውን መቶኛ አረቦን ድርጅቱ አስከፍሎ ንብረቱን በተጨማሪ ሽፋን እንዲካተት በማድረግ ዋስትናው ይራዘማል፡፡
10. የውል ማደሻው አረቦን መክፈያ ወቅት በመድረሱ ድርጅቱ ውሉ እንዲታደስ ማስጠንቀቂያ የመላክ ግዴታ የለበትም፡፡ ድርጅቱ በማንኛውም ጊዜ የ15 ቀናት ማስጠንቀቂያ በሪኩማንዲ ወይም በእጅ ለመድን ገቢው በመስጠት የማስጠንቀቂያ ቀን ከሚያልቅበት ቀን ጀምሮ ውሉን ሊሠርዝ ይችላል፡፡ በመሆኑም ጥያቄ እንደቀረበለት ለቀሪው የዋስትና ዘመን ድርጅቱ መቶኛ አረቦን ለመድን ገቢው ይከፍላል፡፡
ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ ስለ ቤት ሰብሮ ለሚፈፀም ዝርፊያ የሚሰጥ የመድን ዋስትና የቀረበ ማብሪራያ እንጂ በሕግ ፊት የሚፀና ፖሊሲ አይደለም፡፡
|