የሰው ልጅ ኑሮ ለብዙ ያልታሰቡ ችግሮችና አደጋዎች የተጋለጠ ነው፡፡ አደጋዎች የሚመጡበትን ጊዜና መጠናቸውን መተንበይ ማወቅ ከሰው ልጅ አቅምና ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህች ዓለም በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የቤተሰብ ኃላፊዎችና ግለስቦች በእርጅና ጊዜ የሚጦሩበት፣ በሞት ጊዜ ቤተሰቦቻቸውና ተረጂዎቻቸው ችግርን የሚቋቋሙበት፣ ልጆቻቸው እስከተፈለገው ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ድረስ የሚማሩበት የተለያዩ የሕይወት ዋስትናዎች ሲገዙ ይታያሉ፡፡
ሰዎች የሕይወት መድን የሚገዙት ከሞት እንዲያድናችው ሳይሆን ሲሞቱ ገቢያቸውም ከእነርሱ ጋር አብሮ እንዳይነጥፍና የቤተሰቦቻቸው የሕይወት ጣዕምም ሳይጓደል ኑሮአቸውን እንዲገፉ ለማድረግ የሚያስችል አስተማማኝ የገንዘብ ዋስትና ለማግኝት ነው፡፡
ከመባከን ድኖ ለሕይወት ዋስትና የዋለ ገንዘብ በቤተሰብ ደጋፊ መሞት ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን አስከፊ ችግር ለመቋቋም ከማገዙም በላይ በእርጅና ዘመንም አስተማማኝ መጦሪያ ይሆናል፡፡ ሰው ለመኖር መሥራት ለመስራትም ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ ዕድሜ እየገፋ ሲመጣ የመሥራት ኃይል እየቀነሰ ስለሚሄድ በጡረታ መገለልን ወይም የግል ሥራንም ማቆም ያስከትላል፡፡ ገቢ ዝቅ ይላል፡፡ ወጪ ባለበት ይቆማል ወይም ይጨምራል፡፡ ታዲያ የገቢ ልዩነት በምን ይሟላል?
በጉልምስና ዘመን ያልታሰበለት እርጅና አስከፊ ሊሆን ከመቻሉም በላይ ያለፉበትን ዕድሜ መርገም ያስከትላል፡፡ ነገር ግን በሕይወት ዋስትና ዘዴ የተቆጠበ ገንዘብ ካለ ተጠራቅሞ ገቢ በቀነሰበት ጊዜ ማሟያ በመሆን ሕይወት ጣዕምዋን ሳትቀንስ እንድትቀጥል ለማድረግ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከላይ የተጠቀሱትን የሕይወት ዓላማዎች ለማሟላት የሚያስችሉ የተለያዩ ዋስትናዎች አዘጋጅቷል፡፡
|